ምትኬ ወዴት አለሽን! ቁጥር 2

metekee-wadeete-alashene-quthere-2

ካለፈው የቀጠለ…

በሀሣብ ውልብታ፣ በጥርጣሬ ወጀብ እየተመላለስኩ አስባለው። እንዴት ነው የሚሆን ደግሞስ ልቤ አምጣት አምጣት ይለኛል። ታዲያ ከየት ላምጣ ስሟን አላውቅ፣ አድራሻዋ የለኝ… የት እንደምትኖር አልሠማው። ታዲያ እንዲህ በደፈናው እንዴት እፈልጋለው ተፈልጎ ይገኛልስ? እንዲህ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ… ግን መልስ ሣላገኝለት የቀረሁት ነገር ሆኗል። ተዳፍኖ የቀረው ስሜት ሣይጠፋ ዓመትን አስቆጥሯል። ካለፈው ሣምንት ወዲህ ደግሞ አይቼው በማላውቀው አይነት ስሜት ውስጥ ወድቄ ነበር። እያለሁም በሃሳብ ከንፊያለው… ተኝቼም ሀሣቤ አንድ ነው የልጅቷ ነገር… እረፍት መንሣቱ ምን እንደሆነ ግራ ገባኝ ጊዜው ሄዷል አመት የሞላው ሁኔታ ድጋሚ በምናቤ መሠላሰል ጀመርኩ… በሚገርም ሁኔታ 2,3 ጊዜ ቢሯችን መጥታ ቢሆንም አንድም ጊዜ በስርዓት እንኳን አላወራንም… ማውራት ብፈልግም በፍርሃትም፣ በማፈርም ውስጥ የነበርኩት እኔ ጊዜው ሲያልፍ አሁን ነገሩ በይግባኝ ይያዝልኝ… ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምን ይሉታል። ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ማለት ይሄ ነው።

እንደዛም ሆኖ ተስፋ አልቆረጥኩም ያገኘሁትን አጋጣሚ ለመጠቀም ከጀልኩ እንጂ… ደርሶ ለሚያየኝ አንድ ሠው ምን አይነት ጅል ነው የማያውቀውን ይፈልጋልን? ሳይለኝ አይቀርም። አዎ! እኔ ለራሴ እንዲህ አልኩት… ግን ልቀበለው አልቻልኩም ምክንያቱም እንደማገኘው ልቤ በተስፋ ተሞልቷልና… የሚሆነውን በቀጣይነት የማየው ቢሆንም አበክሬ ስጥር የነበረው ስልኩንና የቴሌግራም አድራሻዋን ለማግኘት ነበር… ለዚህ አያሌ የማላውቃቸውን ሰዎች በማህበራዊ ትስስር ሚዲያ አዋርቻለው… ከሷ ማስታውሠውን ምልክት እንዲሆን ለብዙዎች አድርሻለው።

“ጠየም ያለች… ሠውነቷ ደርባባ… ሞላ ያለች እንደውም እንደዚህ የምትማር… በዛ ላይ apparent እኛ ጋር ወጥታ የነበረ…” እያልኩ ዘረዘርኩ… አብዛኞቹ ኧረ አናውቃትም… እኔ እሷ የምትማርበትን ቦታ አይደለም የምማረው… እኔንጃ የሚሉ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎችን አየሁ… በጊዜው በapparent ከመጡት ልጆች መካከል አንዷ የተማረችበትን ቦታ ነግራን ስለ ነበር… የዛን ዩኒቨርሲቲ የቴሌግራም ገፅ መፈለግ ጀመርኩ… ከዛም ውስጥ ያሉትን የግሩፑን ማህበርተኞች እያየው ልቤ ያረፈበትን እየመረጥኩ ማዋራት ያዝኩ። ከዛ ውስጥ አንድን ልጅ ስጠይቅ እንዲህ አልኩት “በዚህ ዓመት ዩንቨርሲቲ በዚህ department እዚህ የሚባል መ/ቤት Apparent የሠሩትን ልጆች ታውቃለህ?” ሲጀመር ቢያውቃቸውስ 50/60 ሠው ስልክ ሊልክልኝ ኖሯል! ልጁም ሣይመልስልኝ ውሎ አደረ… በሌላ ቀን 2 መንትያ እህትማማቾች እዚህ የሚባል ዩንቨርሲቲ ተማሪ ነበሩ እኛ ጋር apparent የወጡ ታዲያ ታወቃቸው ይሆን አልኩት? አሁንም መልሱን ወዲያው ሣይነግረኝ ቀን አለፈ… በነገራችን ላይ እነዚህን እህትማማቾች በጊዜው የማወቅ እድል የገጠመኝ ከአንደኛዋ ጋር ነበር። እርሱም ቢሯችን ሲመጡ ያየ አንድ እኛ ቢሮ የሚሠራ ልጅ ጠርቶ አስተዋውቆኛል። የት እንደምትማር? ምን እንደምትማር ሣይቅር ብዙ አውርትናል። እኔ የልጁን ነገር መች አጣሁት። ማኖ ሊያሰገባኝ ኖሯል። የደስ ደስ ቢኖራትም እኔ ጋር ያን ያህል የሚባል ፍላጎት አልነበረኝም… ከአንድ ቀን በኋላ አዎ አውቃታለው ብሎ ፃፈ ያንን ሣይ ልቤ… በደስታም፣ በድንጋጤ ድንግዝግዝ አለ።

ከሠዓታት በኋላ የአንዷን መንትያ ስልክ ጋር እንዲህ የሚል መልዕክት ጨምሮ ሠደደልኝ…”ለሚያስፈልገው ቁም ነገር ብቻ ተጠቀም” የሚል። ወዲያው አንድ ሀሣብ መጣልኝ… ለካ ስልኳን ስወስድ የመሠለው ለሌላ ጉዳይ መስሎት እንደሆን ገባኝ። ምናልባት ልጅቷ ብዙ ሠው በዝቶባት ይሆናል… ብዙ ተመላላሽ ታካሚ… ብዙ በውስጥ መስመር ፀሀፊ በዝቷል በቃ አልኩኝ። ከዛም ልጁን በደንብ አመስግኜ ልጁ በሠጠኝ አድራሻ ተጠቅሜ ልጅቷን ደግሞ ማናገር ጀመርኩ እንደተለመደው ወሬዬን ከመጀመሬ በፊት ንግግሬን በሠላምታ አሟሽቼ ስጠብቅ የሷ መልስ ዝምታ ሆነ… እኔም ወደገደለው ሃሳብ ራሴን አስገባው… ስለምፈልጋት ልጅት የማውቀውን የባጡን የቋጡን ቀባጠርኩ… ግን የሷ ምላሽ የነበረው ግን “ውይ ማንን እንደጠየከኝ አላወኩም ወይ ደግሞ ስሟን ብትነግረኝ አድራሻዋን ልሠጥህ እችላለው” አለችኝ። እኔ ደግሞ እንኳን ስሟን አድራሻዋንም አላውቅ… የት ብትለኝ የት እላለው እያልኩ ሃሣብ ማውጠንጠን ጨርሼ እንዲህ የሚል ሀሣብ አሠፈርኩ… “እውነት ለመናገር ስሟን በውል አላውቀውም ግን ከእናንተ ጋር apparent እንደወጣች እስታውሣለው ይሁንና ከእናንተ ግሩፕ ጋር ስትቀላቀል አላኋትም የራሷ ቡድኖች ጋር ታዘወትራለች ራሷን በራስታ ስታይል ትሠራ ነበር አልኳት አክዬም… በመልክም በአቋቋም ይገልፃታል ብዬ የማምነውን ሁሉ ዘረዘርኩ፡፡” ምናልባት ልጅቷን ለማግኘት ከረዳት ብዬ በስተመጨረሻም ልጅቷን እንዳስታወሰቻት ነገር ግን ብዙም እንደማትግባባት ገልፃልኝ ከሷ ይልቅ ጓደኞቿን ስለምታውቅ “እነሱን ልጠይቅልህ እችላለው”አለችኝ። በአንዴ ውስጤ በድንጋጤ ሲርበተበት… በሃሴትም ሲፈድቅ የስሜትን መነባበር መቻል አቅጦት ደርቆ ቀረ።

በነጋታው ከአንድ አንድ ስልኳን ላከችልኝ አላመንኩም በቃ አለም ዘጠኝ ነች አልኩ… ሞኝ የምመስለው እኔ “አበቃ አገኘኋት አልኩ አለቀ” የሚል ቃል ከጆሮዬ ያቃጭል ነበር። ልጅቷን ከልብ አመስግኜ ወደ መጨረሻ መዳረሻዬ በይፋ መድረሴን ለራሴ አበሰርኩት። የስልኳን አድራሻ ምትክ ብዬ ሠየምኩት። በእውኑ ደስም አለኝ፡፡

Comments (0)
No comments yet