ምን ትጠብቃላችሁ!

1 min read
mene-tethabeqaalaacehu

ምን ትጠብቃላችሁ በሚል ርዕስ የተተየበው አጭር መጣጥፍ ከሚያዚያ 12፣ 20 እና ግንቦት 11,2012 ዓ. ም በዘመነ ኮፊድ-19 የተፃፈ ሲሆን ፀሀፊው የትምህርት ቤት ጓደኞቹን እያሰበ በጊዜያት ውስጥ ክስተቶችን አሳላስሎ በትናንትና እና በዛሬ የጊዜ ሚዛን ለክቶ፤ ከጊዜ ሚዛን ላይ የሰፈራቸውን ሁናቴዎች በትናንት ሚዛን ቢለካቸው ከዛሬ ሚዛን በልጠው ታይተውበት ኖሮ ራሱን አዋዷል። ዛሬ ለምኔ የሚል ይመስል ጥላቻው ከዛሬ ፍቅሩን ከትናንት ካደረገ ሰነባበተ። በኮረና ምክንያት ከዩንቨርሲቲ ከተመለስን በኋላ ስለ ትናንት ሁኔታ ስለጓደኞቼ ሳስብ ቆየው። ለምን አልደውልልላቸው ብዬ ስደውል ስልኩ ይጠራል አይነሳም። ደጋግሜ ብደውልም ያው ነው። ላነሱልኝ ልጆች ጋር ደግሞ ሳወራ እንደ ድሮ የሚጫወቱት ልጆች ለምን ደወልክ ሚመስል ስሜት የተመለከትኩ መሰለኝና በጊዜው ተሰማኝ። አሁን መልሼ ሳነበው ምናልባት የስነ-ፅሁፍ አካሄዱና ቃላት አጠቃቀሙ ሳቢ ባይሆንም ትናንትን በጊዜ ውስጥ የኋሊት እንድቃኝ ስላደረገኝ መሰረታዊ የሰዋሰው ለውጥ ሳላደርግ እንደወረደ ለማቅረብ ሞክሪያለው። "በቃል ያለ ይረሳል፤ በፅሁፍ ያለ ይወረሳል" እንዲሉ አበው በጊዜው ከትቤ ያስቀመጥኩትን ከኮመዲኖ ውስጥ አውጥቼ አቧራውን አራግፌ የተቀመጠውን ነፍስ እንዲዘራ ትናንትን ዳግም እንዲዘክር አምጥቼዋለው። በነገራችን ላይ...የፃፍኩት የግል ምልከታዬንና አረዳዴን ነው። መልካም ንባብ።

አንዳንዴ ነገሮች ደግመው ቢመለሱ እላለው። ሁኔታና ጊዜ አለመገጣጠም ሆነና አንድ ክስተት ሳይደገም አንዴ መጥቶ ሲያልፍ ይታያል። በፊት የነበረው ትዝታና ትውስታ እንደ አሽዋ በኖ እና ተኖ ሲጠፋ መመልከት በእጅጉኑ ያሳዝናል። ምናለ አሁን ተመልሼ እንደበፊቱ በሆንኩ ያስብላል። የነበረን ጊዜና ሁኔታ ተገጣጥሞ አንድ ጊዜ ብቻ ሲከሰት ማየት ለካስ መታደል ነው። ተመልሶ አይመጣማ። ለክስተት መፈጠር የጊዜና የቦታ አንድነት ወሣኝነት አለው። ውልደታችን፣ እድገታችንንና፣ ሞታችንም የዚሁ አንድ አካል አንድ አምሣል ነው።

እንዲህ እንድል ያለኝ ነገር ቢኖር በምናቤ ይመላለስብኝ የነበረ ሃሣብ ነው። እንደው ምናለ ነገሮች ተመልሰው ጓደኞቼን ባገኘው፤ ምናለ ተመልሼ ት/ቤት ቦርሳና ምሣቃ ይዤ ብሄድ እላለው። አንደምናውቀው ተማሪዎችን በአንድ ቦታ ሚሰበስበው ት/ቤት ነው። ስለዚህም ጓደኛ 'ሚገኘው ከዚሁ ከት/ቤት ነው። ነገር ግን ጓደኝነታችን በት/ቤት አላልፍ አለና ሀ ብለን ከጀመርነው የአስኮላ ትምህርት እስከ 12 እስክንጨርስ አንድ ላይ ብንሆንም የኋላኋላ ትምህርት ሲያልቅና ሁሉም ወደ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ሲበተን ሁሉም አይንህ ላፈር ሆነ።

ሁሉም ወደራሱ መሯሯጥ ሲጀምር እንኳን መገናኘት በስልክም የእግዚአብሄር ሰላምታ ብርቅ ሆነ። ጓደኝነታችን በት/ቤት የታቀበ ሆነና ሩቅ ማሰብ አቅቶት ቅርብ አዳሪ ሆነ። ጓደኝነታችን አንድ የሆነ አጋጣሚ ሆነና ግጥምጥሞሹ በጊዜና በቦታ ሲለያይ ሁሉም ተለያየ።

ምን ማድረግ ይኖርብን ይሆን?

ግቢ እያለው ሰው መልመድ ከብዶኝ ነበር። ድሮ ከነበረኝ የትምህርት ቤት ህይወት የተለየ ሆነና ብቸኝነትን መረጥኩ።

ወይ ጉድ ብቻ ሲኮን ደሞ ብቻ ማውራትም አለ። ይሁን እስኪ ሰው እስኪገኝና እስክላመድ ለወፉም ለነፋሱም አወራለሁ።

ህይወት ቀጣይ እንደሆነች ምናለ ጓደኝነታችን ቀጣይ ቢሆን እስኪ አንዳንዴ በበአላት ጊዜ እንኳን አደረሳችሁ ብንባባል በአዘቦትም ጊዜ የእግዚአብሔር ሠላምታ ባንከለክል። እንደዋወል፣ እንጠያየቅ የአንዳችን መኖር ለሌላው መሠረት ነውና። ምን ያገናኘዋል እንዳትሉኝ አንበሳም ሚኖረው አጋዘን ሲኖር ነው። እንኳን አንድ ላይ አሣልፈን ቀርቶ ለመበላላት 'ሚሯሯጡት እንስሳት እንኳን እራሱ ላንዱ መኖር ሌላው መሠረተ-ድንጋይ ነው።

በአካልስ ተቀጣጥረን ብንገናኝ ምን አለ?

የእረፍት ጊዜ ካለኝ ከጓደኞቼ ጋር መደዋወል ደስ ይለኛል። አለፍ ካለም ሻይ ለመጠጣት ተቀጣጥረን የመገናኘት ልምድ አለን። ታዲያ ስንገናኝ የባጥ የቆጡን እያወረድን እንጫወታለን። ያሣለፍነውን ነገር እያነሳሳን እንነጋገራለን። ይህ አንድ ግንኙነታችን ማጠንከሪያ ገመድ ነውና።

አንዳንዴ የምደውልላቸው ልጆች ጋር ስላለፈው ነገር ስንነጋገር ውይ ረስተነዋል ይሉኛል። ቢያንስ የ 2 አመት ታሪክ! እሱም የምርቃታችንን ቀን የነበረውን እኮ ነው። ይህ አንዱ ለነገሮች የምንሰጠው ግምት አናሳ መሆን ነው እላለው። በድምፅ፣ በምስል፣ በተንቀሳቃሽ ምስልም ተጠርዘው የተቀመጡ ነገሮችን መልሼ ስመለከት ውስጤ በሃሴት ይሞላል። መች እንደው ይህንን ተማሪ ባገኝ የሚለው ሃሳብ በአይምሮዬ ከዞረ ውሎ ሠነባብቷል።

የሌሎች ስኬት የኔም አንዱ የህይወቴ ቃና ለውጥ እንደሆነ ይሠማኛል። ታዲያ ምነው እንዲህ መጨካከን ከት/ቤት ባለፈ መልኩ ያለንን ጓደኝነት ማስቀጠል ካለብን ታዲያ ምን ትጠብቃላችሁ? በሠላሙ ጊዜ መገናኘት ካቃተን ይኽው ኮሮና ገባና እንኳን ልንገናኝ ከቤት መውጣትም አቃተን። ጊዜው የጥሞና ነው። የአንቅስቃሴ ጊዜው ገታ ተደርጎ የምታሠብበት ነዋ! እንደው ነገሮች እንደገና መልሠው እንደማይመጡ ስመለከት ይቆጨኛል።

* * *

ሰኮንድ- ደቂቃን- ደቂቃ- ሰዓትን-ሰዓት ቀንን እንደወለደ ሄዶ ክስተቶች በጊዜ ውስጥ ሲወድቁ ሲነሱ፣ ሲወጡ ሲወርዱ፣ ሲወለዱ ሲሞቱ ማየት የጊዜ ተፈጥሮአዊ ኃይል ምን እንደሆነ ለማወቅ አያዳግትም። እግዚአብሔር ጊዜን ከፈጠረ በኋላ የክስተቶች ልዕልና ህልፈት የሚያልፍበት ሆኖ ዝነተ-አለም ይኖራል። የማታ እንጀራ ይስጠን፣ ድሌ ማታ ነው ድሌ ሲባል ስሠማ ከዘፈን ማድመቂያ ባሻገር ምንም ሌላ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም ነበር። ለካስ ድሮ በሰው ተከብቤ ስስቅ ስጫወት ተፅእኖ ፈጣሪ የሆንኩ ያህል ይሠማኝ ነበር አሁን ግን ስልክ እንኳን ሲደወልላቸው እንኳ ማንሳት ከብዷቸው አየው። ምን እንደሆነ ባላውቅም ከዚህ በፊት እደውልላቸው እንደነበረ አስታውሳለው።

ሁኔታና ክስተት በጊዜ ውስጥ ተሠድረው ወደፊት ሽምጥ እየጋለቡ ሲሮጡ ከፍጥነቱ ባሻገር በጊዜ ውስጥ መክበርም መሠዋትም አይቀርም። አንዳንዴ የምደውልላቸው ልጆች ጋር ስነጋገር ድምፃቸው ተቀይሮ የማውራት ፍላጎታቸው ቀንሶ ቻው! ቻው! ብለው ለመዝጋት ሲቸኩሉ ይገርመኛል። ከዚህ በፊት አብረን ስንማር የነበርን ጥሩ የሆነ ግንኙነት የነበረን ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን ያው የድሮውን ማምጣት ይከብዳል መሰለኝ መቀዝቀዝ ይታያል።

አንድ ሰሞን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ዛሬ ሠው እጅ ላይ ጥሏቸው ስመለከት በቃ የማታ እንጀራ ስጠኝ እላለው። ሁሉም ነገሮች እንደነበሩ ስለማይሆኑ በክስተቶች ላይ የሚፈጠሩት ለውጦች ምክንያት አንዳንዴ ለመቀበል ያዳግተኛል።

ዞሮ ዞሮ በድሮ በሬ ያረሰ የለምና የዛሬውን ጠበቅ ማድረግ ሣይሻል አይቀርም ነገም ለኔ ነውና! በጊዜ ውስጥ በጎ ሁናቴ ይከሰትና መጨረሻም በጥሩ ሁኔታ ላይጠናቀቅ ይችላል። ይሁን ለኔ አንድ ጥሩ ቀን መውጣቱ አይቀርም ያው ሠው ለሠው መድሀኒት ነው አይደል ሚባለው። ሠው ሲርቅና የብቸኝነት ጊዜ ሲመጣ አንዳንዴ ሁኔታዎችን መቋቋም ያቅትሃል። እንኳን በዚህ ጊዜ ተገናኝቶ መጨዋወት ይቅርና ስልክም እኮ ማንሳት ትተዋል። ጊዜ የማናቆመው ተፈጥሮ ስለሆነ ይሄዳል እኛስ ጭኖን መውሰዱ አይቀሬ ቢሆንም እኛ ግን ከጊዜው በላይ ለውጣችን እንደ ጉኖ በኖ ጠፍቷል።

* * *

ተመልሶ በማይመጣ ነገር ላይ ችክ ማለት ወራጅ ውሃን መልሶ እንደማፍሰስ ነው። በሄደ ነገር ላይ ቆሜ አሁን ያለሁበት ጊዜ እያለፈ እንደሆነ ይሠማኛል። ነገሮች ተመልሰው ቢመጡ እላለው ያው ተፈጥሮ ሆነና ወደ ፊት እንጂ ወደኋላ አይገሰግስም። የት/ቤት ተማሪዎች ጋር ከተለያየን በኋላ ስለተነሱ ወቅታዊ ሁኔታ ማወቅ ፈለግኩ። ማለትም የት እንደሚማሩ፤ በአሁን ሠዓት ምን እየሠሩ እንደሚገኙና ወደፊትስ ምን እንዳሰቡ መወያየት ወይም discuss ማድረግ እንዳለብኝ ተሠማኝ ከዛ በተጨማሪም ት/ቤት በነበርንበት ጊዜ የተነሳሁትን ፎቶም መጠየቅ አንዱ አላማዬ ነበር ወደፊትም ይቀጥላል…

ተማሪው ወደ ተለያየ የከፍተኛ ትምህርት ከተበታተነ በኋላ እነሱን በአካል ማግኘት ትልቅ ፈተና እንደሆነ እገምታለው ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያና በስልክ ስላሉበት ሁኔታ መጠየቅ ግን ሣይሻል አይቀርም። በስልክም ከአንዳንድ ተማሪዎች ጋር መነጋገር ችያለው። ጥሩ የሆነ ንግግርም ማድረግ ችያለው ነገር ግን 2 ጊዜ እና ከዛ በላይ ሲደወልላቸው ትንሽ የደበራቸው የሚመስል ንግግር አስተውላለው... አላውቅም ይህ የኔ ግንዛቤ/ የግል አስተያየት ነው።

በህይወት መንገድ ላይ የሚገጥመን ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የሚያልፉን ነገሮች ብዙ ናቸው። ውሃን ሽቅብ እንደማይፈሰው ሁላ ጊዜንም የወደ ኋላ መጎተት ዘበት ነው።

***

በተመሳሳይ የህይወት መንገድ ላይ የነበርን ልጆች ዛሬ መንገዳችንን ተለያይቶ ኑሮ ደግም ላያገናኘን በሚመስል ሁናቴ ተለያይተናል። ግጥምጥሞሽ ካላገናኘን በስተቀር ራሳችን አስበን ላለመገናኘት እንደተማማልን ይመስል ርቀን ሄደናል። ከአንድ ተማሪ ጋር ባደረኩት ረዘም ያለ ንግግር ውስጥ አንዱ የተማሪ ህብረት የመመስረትና ዳግም የመገናኘትን ነገር ማመቻቸት ነበር። ነገር ግን ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ እንዲሉ መጀመሪያስ ያለን ቅን-እሳቤ በቀደመ ነበር። አንዳችን ለአንዳችን ስኬት ደስተኞች ስንሆን ለማገዝም ስንፈቅድ በስልክም ቢሆን የእግዚአብሔር ሰላምታ መለዋወጡ ጥሩ ነበር።

የጊዜ ተቃራኒ ሆኜ መሄዱ ባያዋጣም ቀጥዬበታለሁ። ጊዜ ሲፈጠር ወደፊት ልጓሙን ስቦ እንዲሸመጥጥ እንጂ ወደኋላ እንዲንሸራተት አይደለም። እኔ ግን የነበረን ጊዜ ላይ ሙጥኝ ብዬ ከቆየሁ ሠነባበትኩ። ግን ካለፈው ነገር የቀረኝ ማስታወሻ ብቻ ነው። እኔን እየታየኝ ያለው የወደፊቱ ለውጥ ሣይሆን ያለፈውና የነበረው የአምና ታች አምና ብሂል ነው። ምክንያቱም ለኔ ያለፈው አዲስ ነውና።

ሠዎች የመልካም ምኞት መግለጫ ሲሠጡ አያለው እሰማለው። ነገሮች ግን ካለፈው ሲብስ እንጂ ሲሻሻል አላየሁም። ትላንት አዲስ ምኞት በተመኙት አንደበታቸው መልሠው ሲረግሙ አያለው እንዲያውም ያለፈውን ሲያመሠኑትና የምመጣውን ዓመት የመረቁትን ያህል ሲመጣ ይረግሙታል ውጣልን አዲሱን እንመርቀው የሚሉ ይመስል ይማረራሉ። በዚህ የጊዜ መምጣት መሄድ ውስጥ ጊዜ ሁለት ጊዜ እየተጠራ ይሄዳል ሊመጣ ተመርቆ ሲመጣ ተረግሞ።

Comments (1)
No comments yet