በጊዜ ውስጥ...ጭፍኑን መታበይ

ሠው መሆን ትልቅ ነው፣ ክብር ነው...ይህን ዓለም እንዲያስተዳድር ስልጣን የተሰጠው ሰው ነው። እፅዋቱና እንስሳትን እንዲገዛ ፈጣሪ ችሮታል። እኛ ሰዎች ከተሰጠን በረከት ይልቅ የምሰራው ክፋት ሆኗል....የምንከበረው ከዝና፣ በወርቅ፣ በሀብት ነው። ከሌለህ የለህም እንደሚሉት ነውና ሰውነት ተዘንግቶ ቁስ ሲከበር ሰው መሆን ይረክሳል። ሰው እንሁን ወገን!
ልጄ ሆይ ሠው ሁን! የሚል ቃል በዉስጤ ይመላለሳል። ሠው መሆን ከንቱ የሚለው የአገሬ አባባል ደሞ የሠውነት ከንቱነትን ይነግረኛል። ሠው በሠውነቱ (በአምላክ አምሳል) የተፈጠረበትን ግብሩን ሣይሆን የተቀመጠበትን ወንበር የምናከብር ሆነናል። በአገራችን ባዳ ሆነናል። በህይወት ስንኖር የረከሠው የሠው ልጅ መሆኑን መናገር ለቀባሪ እንደ ማርዳት ነው። ለስልጣን፣ ለክብር፣ ለዙፋን የሚደረግ መንደርደር ሄዶ ሄዶ የሚከብረው፤ የሚያስከብረው ሠው መሆኑን ሣይሆን በዙፋኑ ክብር መከበር፣ በወንበሩ ክብር መወደስን ነው። ሁነታውን በዚህ መንገድ ለመግለፅ መጀመሬ የአስተዳደሩን ካቢኔን ፣ መንግስቱን ወይንም ፖለቲኩን የመቃወም አባዜ ሣይሆን አዚህ የምሠራበት መ/ቤት የገጠመኝ ነገር አንድም ስላስገረመኝ ሌላም በእልህና በንዴት ውስጥ ስለከተተኝ ሃሳቤን በጥቂት ገፅ ልከትብ ወደደኩ። በመ/ቤቴ ውስጥ አንድ ካፌ ትልልቅ ቤቶችን ተከራይቶ ይሰራል። X café ይባላል። ካፌና ሬቶራንት ሲሆን በውስጡ ብዙ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሠራል። የገረመኝን ሃሳብ ከማንሳቴ በፊት የ Rosa Parks ግለ ታሪክ ላስታውስ። ሮዛ በአንድ ባስ እየተሣፈረች እያለ አንድ ነጭ እንድትነሳ ይጠይቃታል እሷም እምቢታዋን ትገልፃለች። “አልነሳም” ትላለች። በኋላም በግድ እንድትወርድ ትገደዳለች። ይህም በኋላ ላይ በ M.L.King የሚመራ ከባድ አመፅ እና አድማ (civil disobedience) ተደርጎ የባሱ ድርጅት እንዲከስር ምክንያት ሆኖ ነበር። በመልኳ ጥቁር መሆን ከሠው እኩል እንዳትታይ ሆነ። ሠው መሆኗ ተዘነጋ። እዚህ ደሞ X café ሁለት የተለያየ ክፍል ተከራይቶ ያለውን ካፌ በፈለግንበት ቤት እየገባን መጠቀም እንችል ነበር። ታዲያ አንድ ቀን አንዱ ቤት ላይ የተለጠፈውን ሥናይ “ከ ማኔጅመንት በስተቀር መስተናገድ አይችልም” ይላል። ነገሩ ገርሞን ቢሆንም ትተነው ሄድን። ነገር ግን ቦታውን አዘውትረን የምንመገብበት በመሆኑ እንዲህ በቀላሉ መነሣት ከበደን። አንድ ጊዜ ልንበላ እየተሠናዳን እያለ አንድ ሴት (በመልክ አስታውሳታለው) ይህ የማኔጅመንት ነው ምናምን እያለች ሽርጉድ ማለት ጀመረች። ይህ አልበቃ ብሏት ውስጥ ገብታ በኛ በኩል መስኮቱን ከውስጥ ማንኳኳት ጀመረች ። ምን ሆና ነው ብለን ዞር ስንል እነ ማኔጅመንት ሱፋቸውን ገጭ አድርገው ወደኛ እየመጡ ነው። እንድንነሣላቸው አይን አይናችንን ያዩናል። ተነስተን ሄድን። እየበላን ቢሆን ኖሮ ምግብ ክቡር ነው አልነሳም ብዬ እንደ ሮዛ ፓርክስ እምቢኝ ማለቴ አይቀርም ነበር። ያው ፉከራ ያያቴ ነው! ዘራፍ። በሌላ ሣምንት ጠዋት ቁርስ ልንበላ ወደ ካፌው ስንሄድ ያ የተለጠፈው ማስጠንቀቂያ ተገንጥሏል። አንጀቴ ነበር የራሰው። እሠይ! አልኩኝ በውስጤ ቦንቦልኖ እስኪደርስ ጠብቄ መምጣቱን ካየው በኋላ አዝዤ ስወጣ ጓደኛዬ ለማኔጅመንት ላይ ላሉት ሰዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠው ካፌ ተቀምጦ ነበርና እኔም ወደዛ ሄድኩ። ቁርሱም መጣና በላው። ሠዓት እስኪደርስ ቁጭ ብለው እያወጋን አንድ ስሙን በወል የማላውቀው እኔ ግን CIA የምለው “ወሬ አነፍናፊ” ስል ይቅርታ አድርጉልኝ ማጋነን አይደለም። “ካድሬ ቢጤ ነው”! CIA እኔ Stalin ከምለው ጀሌው ጋር ሲዞር አየዋለው ምን እንደሚሰሩ አይገባኝም። መንግስት ቤት ቁጭ ብሎ መብላት የለመደ መሆኑን ለማወቅ አይከብድም። Stalin እንደውም የመ/ቤት መኪና ይነዳል። ሹፌር አይመስለኝም፣ ሱፍ ቢጤ ሲለብስ አየዋለው። CIA ግን ከማኔጅመንት ጋር ግንኙነት ያለው ከሠራተኛው ጋር ያለውን እሮሮ፣ ወሬ፣ ምስጢር፣ አሉባልታ፣ ለአለቆቹ አቀባይና አቀባባይ ይመስላል። መ/ቤቱ ውስጥ ከሚነዙ ተራ አሉባልታ መካከል እኔ እንኳን የደረስኩበት የደሞዝ ጭማሪ ነው። ደሞዝ ይጨመራል የሚለው ወሬ በጣዉን ተናፍሶ ነበር። በተለይ ደግሞ ዋና አስተዳደሩ ለቆ ሌላ አዲስ ሠው የሚተካበት ጊዜና እንደተተካ የነበረው የሠው ተስፋ ትልቅ ነበር። በኋላ መልሶ ተነፈሰ። ሌላ ሠው እንደነገረኝ ከሆነ ይህ የደሞዝ ጭማሪ አሉባልታ ከዚሁ በፊትም እንደነበረና ለሠው ቀቢፀ-ተስፋ በመስጠት ብቻ በባዶ ተስፋ እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑን ሠምቻለው። ይህ ሁኔታ ደግሞ አግባብ ባልሆነ መንገድ ስልጣንን ተጠቅሞ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ ሂደትን ያሣልጣል። ይህ ደሞ በሠው ላይ አይፈረድም በተለይ ደግሞ አግብቶ ልጆች አፍርቶ ለሚኖር ወላጅ የቤተሠቡን ህይወት ለማቆየት ከባድ ፈተና ሆኖበታል። ይህ CIA ስራው ወሬ ማመላለስና ማን ለማኔጅመንት ጥሩ ፍቅር ነው ማን ጠላት ነው የሚለውን የሚያጣራ ሰው ነው ሚመስለኝ CIA በግሌ። ወደ ሃሣቤ ስመለስ ቁርሴን በልቼ ከጓደኛዬ ጋር እያወራን CIA በድንገት ሲያልፍ የማኔጅመንት ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ያየናል። ቁጣ ባለው ንግግር ማናገር ፈለገ። ያው ልጆች ናቸው ብሎ ሊያስደነብረን አኮ ነው። እንኳን የሱን ዲስኩር ይቅርና ሰልጣኝ/ ተሠብሣቢ ሲወጣ እንኳን ሣንሠበሠብ ገብተን ሣንሠማ ቁርስና መክሰስ እንክት አርገን የምንበላ። እንደውም አስተናጋጅ ጋር ግልምጫ ዉስጥ ገብተን እንኳ ሣንሠማ የበላን ፈጣጦች። በሠላም ለማዋራት ሞከርን ንግግሩን ሲጨርስ "በቃ ተነሱ" አለ ቁጣ ባለው ድምፅ። ዝም ብለን ያልሠማን መስለን ከዚያም ቆሞ አየንና "እናንተ አትነሱም"… ምናምን ብሎ ማውራት ጀመረ። ኮስተር ብለን ሣናየው ወደ ቢሮ ተመለስን። አንዳንዴ የጠዋት ሲሳይ ቀንህን እንደሚያበራው እንዲህ አይነት ወሬኛ ደሞ ሠው መሆኔን ሊያውን ሠራተኝነትን ዘንግቶ ለአስተዳደሮች ቢያርላቸው አይገርምም። ምናልባት ህግን ማክበር አግባብ ቢሆንም ለምን ብሎ መጠየቅ አይከፋም። ሁሉም በቤቱ እንደሚከበረው ይህ አስተዳደር ውስጥ ያለ ሠው አንድ ሌላ ቦታ ምግብ ቤት ብንገናኝ ተነሳ ሊለኝ ነው። ትራንስፖርት ላይ ቀድሜህ ልግባ ሊለኝ ነው። ስልጣንን መሠረት ያደረገ መታበይ ጊዜ ያስታጠቀው ጊዜ እንደሚፈታው ላንድ አፍታ ቢታየው እንዴት ይሆን? ይህ ሁኔታ ለአስተዳደሩ ያለኝን ክብር አውርዶታል። በዙሪያቸው ያሉት ጃሻ ጃግሬዎች ምናልባት እንጀራቸው ሆኖ ሽርጉድ ሲያበዙ ማየት ቢገርመኝም መኖሪያቸው ስለሆነ አይሰማቸውም። “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንዲሉ ፊታቸውን የጣሉ አስተናጋጆች ጋር ምግብ ማዘዝም መብላትም ለአይን ይደብራል ለማኔጅመንት ሲሆን 32 ጥርሳቸውን ከፍተው የምፅአት ቀንን ያለፍ የመሠላቸውን አስተናጋጆች ምን ይሉታል? ጭራሽ ኩፖን ቆርጬ ለአንዷ አስተናጋጅ ስሰጣት እኔ ማኔጅመንት ጋር ነው ማስተናግደው ለሌላ አስተናጋጅ ስጠው ብላ እርፍ! አንድ ካፌ ሆኖ ሳለ እንዲህ መሆን ምን ይሉታል ። አንድጊዜ ከጓደኞቼ ጋር እየሄድን CIA እና ሌሎች ሠዎች መኪና ተቆልፎባቸው ቁልፍ ውስጥ ስለሆነ ለመክፈት እየታገሉ ነበርና ሁለቱ ጓደኞቼ የሚሰሩትን ቆም ብለው እያዩ መኪናዋ ድንገት ስትጮህ ምንም ያላደረጉትን ልጆች እነሱ ናቸው መኪናውን የነኩት ብሎ ጮኸ። እኔ በቦታው በነበረኩ ምስክር እሆናለው ምንም አላልኩም ነበር። እኔም ጓደኞቼም ተናደው ምን አይነት ብለን ታዝበን ከግቢ ወጣን።።