ምን መሰላቹ. . .

mene-masalaacu

ዓለሚቱ አጥብቀው ከያዙት ለቀቅ ላደረጉት ዛፍ ፥ ለሞኝ ከሚያሳዩት ለብልህ ለነገሩት ታሪክ ታደላለች።

መስከረም 1 ብዬ ጓጉቼ፡ ተጎዝጉዤ ተቀበልኩ። ከዛ እንዲው እንደቀልድ መስቀል ላይ ደረስኩ። መስቀል ቀኔ ነው። የተወለድኩበት ዕለት። ታዋቂ አርቲስቶች የተወለዱበት የሆኑት ያገቡበት ከዛ ደሞ የሞቱበት ያው የእኔም ልደት።  በዚው አጋጣሚ የአለምን እርግጠኛ ባልሆንም የሀገሬ ጥበብ ግን እንደጠራቺኝ ለማሰወቅም ነው። እና ዕድሜዬን፡ የአመቱን ለውጥ፡ የጊዜውን ፍጥነት ስመለከት እስኪ አንዴ ቆም ብለሽ አስቢ አስቢ አለኝ። 

ሶ ምን መሰላቹ ማደግ፡ ለውጥ እና ጉልምስና የማይጥሙኝ ሰው ነኝ ህዝባር ነበርኩኝ። የልጅነት ጣዕምንም ያን ያህል የማውቀው አይመስለኝም ግን እንዲው ከማደግ ልጅነት ይሻላል ብዬ አምናለው። እና ምንም ባለማድረግ ውስጥም ሆነ በመሯሯጥ ውስጥ ያየሁት ነገር ቢኖር ይቺ ኑሮ ላይ ዘላቂም፡ ቋሚም፡ አዲስም ነገር እንደሌለ ነው። ይመስለናል እንጂ ከልኬቱ እና ከቀኑ የሚያልፍ ነገር የለም። ቀን በቀን ሲለወጥ ብዙ ይረሳል፡ የሄደም ይተካል። የማይለያየው ተጣልቶ፡ የማይተዋወቀው ተፋቅሮ፡ የማይመጣው ተከስቶ ብቻ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል። 

የዚን ዙርያ እኩሌታውን ማግኘት ቢከብድም እንዲው ሳየው ሳየው ግን 'በአግባቡ ንቆ መተው' የተሻለ ይመስለኛል። ለምሳሌ አንዴ አንዷ ጓደኛዬ ትንሽ ቀላል ያለ ቲያትር አሰራቺኝ። ቲያትሩ ይደብር ነበር፡ ግን ደግሞ መውረጃውን አክብጄ አየሁት። ደግሜ ደጋግሜ ተውንኩበት። ሳየው ግን እኔ ደከምኩ እንጂ ልብ ብሎም ያየኝ አልነበረም። ጭብጨባ ስጠብቅ ጭራሽ ተሳቀብኝ። ከዛ ያው ሳልወድ በግድ ከመድረኩ ወረድኩ። አሁን የዛኔ የልጅቷን መራሄ ተውኔትነት በአግባቡ ተረድቼ መተወን ይለፈኝ ብል ኖሮ ከተመልካች እጥረት የመጣብኝን የትንሽነት እና ምንምነት ስሜት አሸንፍ ነበር። 

ምሳሌ 2፡ አንድ ለምን እና እንዴት እንደወደድኩት የማላውቀው ሰው ነበር። እኔው ግራ ገብቶኝ እኔው ሳስረዳ ከረምኩ። ስችል በንግግር ሲያቅተኝ በጽሁፍ ለማስረዳት ጣርኩ። መሪ ጌታ ጋር ሄዶ ያሰራብኝ እስኪመስለኝ ድረስ እንደጦስ ዶሮ ዞርኩት። እንደሞኝ ለቅሶ ሳላዝን ከረምኩ። ሰውም ጆሮውን እየያዘ ሮጠ፡ እሱም አለ'ም የለም ሳይባል ብቅ ጥልቅ እያለ ቆየ። ብቻ 'ጊዜ ጸሃይ' በጥራት አሳየኝ፡ ልብ ብዬ ሳየው ያስደገመብኝ መሰለኝ እንጂ  እሱ ጸሎትም ወደ እኔ ዞሮ አልጸየም። ያኔ ገብቶኝ ቢሆን ኖሮ ይህም ያጋጥማል በሚል መረዳት ዞወር ማለት እችል ነበር።

ምሳሌ 3፡ ብዙ እኔ ላይ ብቻ የሆኑ የመሰሉኝ አጋጣሚዎች፥ ለእኔ ብቻ የከፉ የመሰሉ ቀናት ነበሩ። ንጋት ያስጠላኝ ጸሃይ ያንገሸገሸኝ ሰላም የናፈቀኝ ዘመን ነበር። ስለዛሬ ቢነገረኝ ኖሮ የማላምንበት፥ የአመቱ ቁጥር ቢጨምርም የእኔ ግን እዛው የቀረበት ጊዜም ነበር። ባላምንበትም ባይመስለኝም ነገ ሌላ ቀን እንደሆነ ባስብ ኖሮ ዛሬ ላይ ጊዜዬን በጥገና አላሳልፍም ነበር። 

ምሳሌ 4፡ እሷ እንኳን ሁሌም ትደርስለኛለች፥ እሱ እንኳን ካለእኔ አይተነፍስም፥ እነሱ እንኳን ያለእኔ አይቆዩም ያልኳቸውም ሆነ እኔ አልረሳቸውም ያልኳቸው ሰዎች፡ ስማቸው ሲጠራ በቀጥታ የዕንባ ቀረጢቴን የሚያንኳኩ ሰዎች ዛሬ ላይ ከትናንትና ጋር አብረው መቅረታቸውን ሳይ ምነው ያኔ ላይ ይሄንንም ባሰብኩ እንድል ያደርጉኛል።

የማሰላሰያ እና የመጻፊያ ጊዜ ቢበቃኝ ኖሮ ብዙ ምሳሌዎች ሰፋ ካሉ ማብራሪያዎች ጋር የማቅረብ ብቃቱ ነበረኝ፡ ያው ዕድሜም ይፈቅድልኛል፡ ዕለቱም ጭምር። ግን አንድ ነገር ግልጽ ነው። ህይወት ብትከብድም አትቀልም፥ ብታስከፋም አታስደስትም፥ ብትሞላም አትተርፍም፥ ብትጻፍም አታልቅም፥ ብትብራራም አትገባም፥ የልኳን ያህል ግን ተኑራ ታልፋለች። ለሚሆኑት ነገሮች ቀለል አድርጌ ግን በቂ ትኩረት ሰጥቼ በመጨረሻም ንቄ ትቼ የማለፍ አቅሙ ቢኖረኝ ኖሮ ዓለም ላይ መቆየት ጥበብ አይሆንብኝም ነበር። ሰው መሆን ራስን ከመቆጣጠር የዘለለ ሃላፊነትም ስልጣንም እንደሌለው ብረዳ ኖሮ ሁሉን ካልያዝኩ ካልጨበጥኩ አልልም ነበር። የእንግዳነት ዘመኔን እንደ ህያው ፍጡር ባልተጠበብኩበት ነበር። ብቻ ምን ለማለት ነው፡ መልካም ልደት ለእኔ ሚዛናዊ ህይወት ለእናንተ። 

Comments (1)
No comments yet