አፋልጉኝ

Billie Eilish's 'What was I made for?' made me write this.
በመገናኛ በኩል በብዛት አልፋለው። ጭንቅንቅ ያለ ቦታ ነው እንደ ስሙ ሁሉም የሚገናኝበት ቦታ ነው። ከሰው ጋር ተጋፍቼ የምሄድበት ቦታ ነው፣ ከብዙ ሰው ጋር። ለመቆም እና ረጋ ብሎ ለመራመድ የማይመች ሰፈር ነው። በዛ ሁሉ ግርግር መሃል በብዛት የሚያጋጥመኝ በእድሜው ገፋ ያለ ሰው አለ። መሀል መገናኛ ላይ ብዙም የማይሰማ ሙዚቃ ይጫወታል። ጠቆር ያለ ሰው ነው ጸሀዩ ሲጨመርበት ደግሞ ፊቱ እርር ይላል። ክራር እና ሌሎች ስማቸውን የማላውቃቸው መሳሪያዎች ይዞ ይጫወታል። አፉ ጋር አንድ የታፈነ ድምጽ ማጉያ ያደርጋል። ከዛ ይዘፍናል። ሁሌም የምመኘው ግን አድርጌው የማላውቀው አጠገቡ ቁጭ ብዬ አላፊ አግዳሚውን ማየት ነበር። እሱ ይዘፍናል፣ እኔ አያለው። እሱ በሚያደርገው ነገር ደስተኛም ተስፈኛም ይመስላል። ጥቂት ሰዎች ገንዘብ ይሰጡታል። የኔ ቢጤ ሯጭ ደግሞ አይቶ ብቻ ያልፋል። ቦታው የተመቸው ይመስላል። ሰው ሁል ወደ መዳረሻው እየተጋፋ ሲጓዝ እሱ እንደማይሰማ የሚያውቀውን ሙዚቃ ይጫወታል። ዓለም ላይ ምን እያመለጠኝ ይሆን ብሎ አይጨነቅም። ሰዉ ይሮጣል፣ ይጋፋል፣ ይቸኩላል። እሱ ቁጭ ብሎ ይዘፍናል። ብዙ ግዜ ፈገግ ይላል። በዛ ሁሉ ጸሃይ ሳይደክመው ይጫወታል።
ዓለም ለእኔ መገናኛን ትመስለኛለች፣ ጭንቅንቅ ያለች ግፍያ የበዛባት ሁሉም የሚያልፍባት። መገናኛ ላይ መቆም እና መረጋጋት እንደሚከብድ ሁሉ ዓለምም ላይ ረጋ ማለት እፎይ ማለት በጣም ጭንቅ ነው። ሁሌ ሩጫ ነው። እኔ አልሮጥም ብል እንኳን መገፍተሬ ከመንገዱ ዞር በይ መባሌ የማይቀር ነው። እኔን ገፍትሮ ያለፈው ሰውዬ ለመሙላት አንድ ሰው የቀረው ታክሲ ውስጥ ሮጦ ተሳፍሯል። ታክሲ ከዛ በኋላ ይኑር አይኑር፣ ይቆይ አይቆይ ግን አላውቅም። ምናልባትም ፈጥኜ ብራመድ ኖሮ የሞላው ታክሲ የኔ መሳፈሪያ ይሆን ነበር። ዓለም ላይ ያሉ ዕድሎችም እንደዛ ታክሲ እያመለጡኝ ይሆን ብዬ አስባለው፣ እፈራለው። መገናኛ እና ዓለም ለእኔ አስጨናቂ ቦታዎች ናቸው። ሁለቱም ያንገላቱኛል ግን ደሞ ቦታዬን አይነግሩኝም። ሁለቱንም ማለፌ ግድ ነው ግን ደግሞ ወንበሬን አያሳዩኝም። በሰው መሃል እጓዛለው፣ እጋፋለው፣ እሮጣለው ግን መቼ እንደሚያልቅ፣ እንደሚያበቃ አላውቀውም። ቆሜ እንዳስብ እንድተነፍስ አይፈቅዱልኝም።
ዓለምን እና መገናኛን የቀደማቸው ግን ያ ዘፋኝ ይመሰለኛል። ሁላችንም ስንሮጥ እሱ አንድ ቦታ ላይ ቁጭ ብሏል። አብዛኞቻችን ዓለም ምን እንደምትሰጠን ሳናውቅ እሱ ግን ለዓለም ደስ የሚለውን ነገር እየሰጠ ነው። ለምን ይሆን የተፈጠርነው ብለን ስንወዛገብ እሱ ክራሩን ይዞ ይጫውታል፣ ለዛ ነው የተፈጠርኩት ብሎ ይኖራል። ጸሃይ ያውም የምስራቅ አፍሪካ የምድር ወገብ ጸሃይ አይበግረውም። ድምጼ አያምርም፣ የምለው አይሰማም ብሎ ከመዝፈን አልተቆጠበም። መገናኛን የሚያህል የተጨናነቀ ሰፈር ውስጥ ቁጭ ብሎ ይዘፍናል። ከዓለም ጋር የሚያካሂደው ጥያቄ እና መልስም ፣ የሚያወራርደው ሂሳብም የለበትም። የውስጡን፣ የልቡን ባላውቅም እሱ ዓለምን በልጧታል። ቦታውን ወንበሩን አግኝቷል። እኔስ? What was I made for?